አታላንታ እና ኢንተር የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎን አግኝተዋል፡፡
የ2018/19 የጣሊያን ሴሪ ኤ የመጨረሻ ሳምንት መርኃግብር ጨዋታዎች በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ተካሂደው በመጨረሻም የአውሮፓ ውድድሮች ተሳትፎ የሚያገኙ ቡድኖች እና ከሊጉ ወራጅ የሆኑ ክለቦች ተለይተው ታውቀዋል፡፡
ትናንት በተካሄዱ በርካታ ግጥሚያዎች፤ አታላንታ በሜዳው ስታዲዮ አትሌቲ አዙሪ ደ ኢታሊያ ላይ ሳሶሎን አስተናግዶ ከመመራት ተነስቶ 3 ለ 1 በሆነ ውጤት ድል በማድረግ በ112ኛ ዓመት ታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎን አግኝቷል፡፡
ኮሎምቢያዊው ዱቫን ዛፓታ፣ አጥቂው ፓፑ ጎሜዝ እና አማካዩ ማርዮ ፓሳሊች ለቤርጋሞው ቡድን የማሸነፊያ ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል፡፡
በዚህም በአሰልጣኝ ጂያን ፔሮ ጋስፔሬኒ የሚመራው ቡድን አታላንታ ያለፉት ሁለት ዓመታትን ቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ ጫፍ እየደረሰ ሳይሳካለት የቀረበ ቢሆንም፤ አሁን ግን ቡድኑ በ69 ነጥብ ከኢንተር በተሻለ የግብ መጠን ተገኝቶ ሶስተኛ ደረጃን ላይ ተቀምጧል፡፡
ኢንተር ሚላን ደግሞ በሜዳው ጁሴፔ ሚያዛ ኬይታ ባልዴ እና ራጃ ናይንጎላን ጎሎች ኢምፖሊን 2 ለ 1 በማሸነፍ አራተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቅቋል፡፡ ሴሪ ኤው በዚህ ዓመት አራት የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ኮታ በመያዙ ኢንተር ቀጥታ ተሳታፊነቱን አረጋግጧል፡፡
ኤስ ሚላን ደግሞ ከሜዳው ውጭ በስታዲዮ ፓውሎ ማዛ ስፓልን በፍራንክ ኬሲ ሁለት እና ሃካን ካልሃኖግሉ ተጨማሪ ግብ 3 ለ 2 ድል አድርጎ በ68 ነጥቦች የዩሮፓ ሊግ ተሳትፎን አረጋግጧል፡፡
ሮማ ደግሞ በስታዲዮ ኦሊምፒኮ በሎሬንዞ ፔሌግሬኒ እና ዲዬጎ ፔሮቲ ጎሎች ፓርማን በ2 ለ 1 ውጤት አሸንፏል፡፡
የሴሪ ኤው ሻምፒዮን ዩቬንቱስ ወደ ሉይጂ ፌራሪስ አቅንቶ በሳምፕዶሪያ 2 ለ 0 ተረትቷል፡፡ ግሬጎሪ ዴፍሬል እና ጂያንሉካ ካፕራሪ የጎሎቹ ባለቤቶች ናቸው፡፡
በሌሎች ግጥሚያዎች ቶሪኖ ላትሲዮን 3 ለ 1፣ ዩድኒዜ ካሊያሪን 2 ለ 1 ድል ሲያደርግ፤ ፊዮረንቲና ከጂንዋ ያለግብ በአቻ ውጤት ተጠናቅቋል፡፡
ቅዳሜ ዕለት ቦሎኛ ናፖሊን 3 ለ 2 ሲረታ፤ ፍሮሲኖኔ ከኬቮ በዜሮ አቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡
በአጠቃላይ በሴሪ ኤው የ2018/19 የውድድር ዘመን ዩቬንቱስ፣ ናፖሊ፣ አታላንታ እና ኢንተር ሚላን የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎን ሲያረጋግጡ፤ ኤስ ሚላን ሮማ እና ላትሲዮ ደግሞ በዩሮፓ ሊጉ ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡
ኢምፖሊ፣ ፍሮሲኖኔ እንዲሁም ኬቮ ከሴሪ ኤ ተሰናባች ሁነዋል፡፡ ብሬሽያ እና ሌስ ከሴሪ ቢ ወደ ዋናው ሊግ ያደጉ ቡድኖች ናቸው ሶስተኛ ክለብ እየተጠበቀ ነው፡፡