ኢምፔሬያሊስቶችን አደብ ማስገዛት የሚቻለው ወታደራዊ አቅምን ባማሳደግ ነው-ኪም ጆንግ
አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 19 ፣ 2014 ኢምፔሬያሊስቶችን አደብ ማስገዛት የሚቻለው ወታደራዊ አቅምን ባማሳደግ ነው-ኪም ጆንግ ፕሬዚዳንት ኪም ጆን ኡን ሀገራቸው የሚሳኤል ጦር መሳሪያ ትጥቋን ይበልጥ ለማዘመን ማቀዷን ይፋ አደረጉ፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥ 12 የሚሳኤል ሙከራዎችን ያደረገችው ፒዮንግያንግ ሰሞኑን አህጉር አቋራጭ የባለስቲክ ሚሳኤል በተሳካ ሁኔታ መሞከሯ በአሜሪካና አጋሮቿ ዘንድ ስጋትና ቁጣን ቀስቅሷል ነው የተባለው፡፡
ዋሶንግ 17 የተባለው ይህ ሚሳኤል የኒውክሌር አረር ቢገጠምለት በየትኛውም የአሜሪካ ክፍል ጥቃት ማድረስ እንደሚችል ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ ይህ ረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤል ከ6 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ በሆነ ከፍታ 1 ሺህ 90 ኪሎሜትሮችን በ67 ደቂቃዎች ተጉዞ በኮሪያ ልሳነ ምድርና በጃፓን መካከል በሚገኘው የውኃ አካል ማረፉ ተረጋግጠጧል፡፡
ፕሬዚዳንት ኪም ጆንግ ኡን በዚህ አይግረማችሁ፤ ሀገሬ የውጊያ አቅሟን ከፍ ለማድረግ ገና ከዚህ የበለጠ ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎችን ታመርታለች ስራ ላይም ታውላለቸች ብለዋል፡፡ የሀገሪቱ የዜና ወኪል ባለስልጣናቱን ጠቅሶ ባሰራጨው ዘገባ ሰሜን ኮሪያ ሩቅ በማይባል ጊዜ ውስጥ የኒውክሌር ሙከራ ልታደርግ እንደምትችል ጠቁሟል፡፡ በሚሳኤል ሙከራው ወቅት ፕሬዚዳንት ኪም ባስተላለፉት መልእክት ኢምፔሬያሊስቶችን አደብ ማስገዛት የሚቻለው ወታደራዊ አቅምን ባማሳደግ ብቻ ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡ ሰሜን ኮሪያ ባለፈው ሳምንት ያስወነጨፈችው ሚሳኤል እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ከ2017 ወዲህ ተሞክሮ የማያውቅና በአደገኛነቱ ቀዳሚው ነው ሲል አልጀዚራ ዘግቧል፡፡