loading
ከ4 ሚሊዮን 7 መቶ ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው 6 መቶ 38 ሳጥን ቢራን ከጫኑት ተሽከርካሪዎች ጋር ሰርቀው ሊሰወሩ የነበሩ ተጠርጣሪዎችን መያዛቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 14፣2013  ከ4 ሚሊዮን 7 መቶ ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው 6 መቶ 38 ሳጥን ቢራን ከጫኑት ተሽከርካሪዎች ጋር ሰርቀው ሊሰወሩ የነበሩ ተጠርጣሪዎችን መያዛቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ወንጀሉን የፈፀሙት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ልዩ ቦታው አዲሱ ሚካኤል ገነት ህንፃ ተብሎ በሚጠራው የቢጂ. አይ ኢትዮጵያ ምርቶች ወኪል አከፋፋይ አልታድ ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ከሚባል ድርጅት ውስጥ ነው።

አንደኛው ተከሳሽ ተረኛ ጥበቃ መሆኑን እንደ ምቹ ሆኔታ በመጠቀም አብሮት የሚያድር ተረኛ ባልደረባው እረፍት እንዲያደርግና እሱ እየጠበቀ እንደሚያድር አግባብቶት ከሥራ እንዲቀር ካደረገ በኃላ ቀደም ሲል ከድርጅቱ በስነ-ምግባር ከተሰናበተ ግለሰብ ጋር በመሆን ከ4 ሚሊዮ 7 መቶ ሺህ ብር በላይ የዋጋ ግምት ያላቸው 6 መቶ 38 ሳጥን ቢራን ከጫኑት ተሽከርካሪዎች ጋር ሰርቀው ከተሰወሩ በኃላ ንብረቱን በ1 ሚሊዮን 9 መቶ ሺህ ብር እንደሚሸጡት እና ገዥ እያፈላለጉ ስለመሆኑ ፖሊስ ከህዝብ በደረሰውን ጥቆማ እና ባደረገው ክትትል ግለሰቦቹን ከጫኑት ቢራ ጋር በቁጥጥር ሥር አውሏቸዋል፡፡

የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አንበርብር ክንፈ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር ባደረጉት ቆይታ በሰጡት አስተያየት ተጠርጣሪዎቹ መያዛቸው ቢያስደስትም ግለሰቦቹ ተሽከርካሪዎቹን ከቆሙበት አስነስተው ሲወጡ በድርጅቱ ለጥበቃ ተግባር የተገጠሙ የደህንነት ካሜራ ምስሎች ለተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር
መዋል ሚናቸው ከፍተኛ ነበር ብለዋል፡፡

ወንጀል ፈፅሞ ከተጠያቂነት የሚድን ባይኖርም የድርጅት ሃላፊዎች የሚቀጥሯቸውን የጥበቃ ሰራተኞች የሥነ ምግባር ሁኔታ በመቆጣጠር ተገቢውን ክትትል ማድረግ እንደሚገባ ፖሊስ አሳስቦ በተጠርጣሪዎቹ ላይ የሚደረገው የምርመራ ሂደት ሲጠናቀቅ ለሚመለከተው የፍትህ አካል እንደሚቀርብ የአዲስ አበባ
ፖሊስ አስታውቋል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *