loading
ክርስቲያኖ ሮናልዶ በታክስ ስወራ ወንጀል የተፈረደበትን የሁለት ዓመት የገደብ እስር ተቀብሏል

ክርስቲያኖ ሮናልዶ በታክስ ስወራ ወንጀል የተፈረደበትን የሁለት ዓመት የገደብ እስር ተቀብሏል

የ33 ዓመቱ ፖርቱጋላዊው አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ የጥፋተኝነት ውሳኔ የተፈረደበት በሪያል ማድሪድ ክለብ በነበረበት ወቅት ከታክስ ጋር በተገናኙ በሰራው ወንጀል ሲሆን ጥፋተኝነቱን ተቀብሏል፡፡

ፖርቱጋላዊው ተጫዋች ዛሬ በስፔን መዲና ማድሪድ ፍርድ ቤት ከመቅረቡ በፊት ከምስል መብት ካገኘው ገቢ የሀገሪቱን ባለስልጣናቱን በማጭበርበር ወንጀል ፈፅመሀል ተብሎ ምርመራ ሲካሄድበት እና የፍርድ ሂደቱም ሲታይ ነበር፡፡

ያኔ በ2017 ሮናልዶ ከታክስ ስወራ ጋር ስሙ ተያይዞ ሲነሳ ከገቢው ላይ የሚጠበቅበትን የግብር ግዴታ መወጣቱንና በፍፁም የታክስ ስወራ ተግባር ፈፅሞ እንደማያውቅ ተናግሮ ነበር፡፡

የሀገሪቱ አቃቢ ህግ ግን ከ2011 እስከ 2014 በነበረው ጊዜ ውስጥ አራት የታክስ ስወራዎች በተጫዋቹ እንደተፈፀመ አስታውቋል፤ ሮናልዶ ግን የተደበቀው 14.7 ሚሊየን ዩሮ ወይንም 13 ሚሊየን ፓውንድ ከስፔን ውጭ በሚገኙ የታክስ ጉዳዮችን የያዙለት ድርጅቶች ይጠየቁበት ብሏል፡፡

በክሱ ውስጥ በ2009 ከማንችስተር ዩናይትድ ወደ ሪያል ማድሪድ ከተዛወረ በኋላ ይከፈለው የነበረው ደሞዝ ጉዳይ አልተመለከተም ተብሏል፡፡ በዛሬው ዕለትም ፍርድ ቤቱ የክሱን ሂደት በተመለከተበት ወቅት ሂደቱን ለመከታተል ዳኛው ፊት ቀርቧል፡፡

ስፔን ውስጥ አንድ ዳኛ ለመጀመሪያ ጊዜ የተወነጀለን ሰው የሁለት ዓመት የዕግድ እስር የመፍረድ ሰልጣን ያለው ሲሆን ተጫዋቹ በ2018 ከሀገሪቱ አቃቢ ህጋውያን እና ከሚመለከተው የታክስ ባለስልጣናት ጋር ስምምነት መፈፀሙን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ የፈረደበትን የ23 ወራት የቅጣት ውሳኔ ተቀብሎታል ተብሏል፡፡

በዚህም ወደ 17 ሚሊየን ፓውንድ የሚጠጋ የገንዘብ ቅጣት ሊከፍል እንደሚችል ተገልጧል፡፡

የ33 ዓመቱ ፖርቱጋላዊ ፍርድ ቤት የቀረበው ዳኛው የፍርድ ሂደቱን በቪዲዮ ስርጭት እንዲከታተል ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ ካደረጉበት በኋላ ነው፡፡

የሮናልዶ ሰሞንኛ የማድሪድ ቆይታ ይራዘማል ተብሎ የማይጠበቅ ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ ከታክስ ባለስልጣናቱ ጋር አስቀድሞ ስምምነት መፈፀሙን ተከትሎ ነው፡፡

የቀድሞ የክለብ አጋሩ ስፔናዊው ዣቪ አሎንሶ ግን የተከፈተበትን ክስ ማብቂያ ለማበጀት ጊዜ ሳይወስድበት እንደማይቀር እየተነገረ ሲሆን ተጫዋቹ ከ2010 እስከ 2012 ጊዜ ውስጥ የ2 ሚሊየን ዩሮ የታክስ ማጭበርበር ክስ ቀርቦበታል፡፡

ክሱ እንደ ሮናልዶ ሁሉ ከምስል መብት ጋር የተገናኘ ገቢ ስወራ እንደሆነ ተገልጧል፡፡ ስፔናዊው የቀድሞ ተጫዋች የተከፈተበት ክስ ለአምስት ዓመታት እስር ሊዳርገው እንደሚችል እንዲሁም ቀደም ሲል ከከፈለው የአራት ሚሊየን ዩሮ ገንዘብ በላይ ቅጣት ሊጣልት እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡

የ37 ዓመቱ የቀድሞ የሊቨርፑል ድንቅ አማካይ ከተጫዋችነቱ ራሱን ያገለለው በ2017 ሲሆን ምንም አይነት ጥፋት አለመስራቱን መናገሩ ይታወሳል፡፡

ሮናልዶ እና አሎንሶ በስፔን የታክስ ባለስልጣን ምርመራ የተደረገባቸው የመጀመሪያ የእግር ኳስ ሰዎች አለመሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን ከዚህ ቀደም ሊዮኔል ሜሲ፣ ዦዜ ሞሪንሆ፣ሀቪዬር ማስቼራኖ፣ ማርሴሎ፣ ሉካ ሞድሪች፣ አሌክሲስ ሳንቼዝ፣ ሪካርዶ ካርቫልሆ፣ አንሄል ዲ ማሪያ፣ ራዳሜል ፋልካዎ እና ፋቢዮ ኮንትራዎ በተመሳሳይ ክስ ስማቸው የተነሱ ናቸው ሲል Goal.com አስነብቧል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *