loading
ወደ ሀገር ዉስጥ ሊገባ የነበረዉ ገጀራ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2013  ሀሰተኛ ሰነድን ተጠቅሞ ወደ ሀገር ዉስጥ ሊገባ የነበረው የእጅ ገጀራ ተያዘ
የገቢዎች ሚኒስቴር እንዳስታወቀዉ ከ15 ቀን በፊት በአስመጪ ዳዊት የማነ ስም ብዛቱ አንድ መቶ 86 ሺህ 240 የሆነ የእጅ ገጀራ በአራት ባለ 20 ጫማ ኮንቴይነሮች ከቻይና ተጭኖ ሞጆ ጉምሩክ ተጓጉዞ ከደረሰ በኃላ ተይዟል፡፡

እቃው ወደ ሀገር ዉስጥ እንዲገባ ከፌዴራል ፖሊስ የተፈቀደለት በማስመሰል እና ሐሰተኛ ሰነድ አዘጋጅቶ ለገቢ ዕቃ አወጣጥ የሰነድ መርማሪው አቅርቦ ሰነዱ ተመርምሮ ከ7ነጥብ 7ሚሊዮን ብር በላይ ቀረጥና ታክስ ከፍሎ እቃው ከተለቀቀ በኃላ በጉምሩክ ኮሚሽን እና በሞጆ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኢንተለጀንስ በኩል ክትትል ተደርጎ የቀረበው ሰነድ ሲጣራ ሐሰተኛ እና እቃዉም ወደ ሀገር ዉስጥ እንዲገባ ከፌዴራል ፖሊስ ፈቃድ ያልተሰጠው መሆኑ መረገገጡን ሚኒስቴሩ አስታዉቋል፡፡

ጉዳዩ ከ15 ቀን በፊት የተፈጸመ ቢሆንም፤ አስመጪው ያቀረብኩት ሰነድ ህጋዊ ነው በማለት ቅሬታ ስላቀረበ ከፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጋር በጋራ ሲጣራ ቆይቶ በተደረገው ማጣራት ሰነዱ ሐሰተኛ እና ከፌደራል ፖሊስ ፍቃድ ያልተሰጠው መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ በተጨማሪም በጉምሩክ ኮምሽን ሰራተኛ የእጅ ገጀራው ተገቢውን የጉምሩክ ስነ-ስርዓት በመፈጸም እንዲስተናገድ የሚገልጽ ሐሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት ለማውጣት የተሞከረ ሲሆን ይህም ሐሰተኛ ሆኖ
ተገኝቷል፡፡

ይህን መነሻ በማድረግም በፌዴራል ፖሊስ ለሞጆ የወንጀል ምርመራ ማስተባባሪያ ፅ/ቤት መረጃዉን በመስጠት በተደረገው እልህ አስጨራሽ ክትትል የእቃው ባለቤት እና ትራንዚተሩ ተይዘው ጉዳዩ በምርመራ ላይ ይገኛል:: ገጀራ ክልከላ ከተደረገባቸው እቃዎች አንዱ ሲሆን ከፌደራል ፖሊስ ሕጋዊ ፈቃድ ሳያገኙ ማስገባት የተከለከለ ነው፡፡ በአንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በጉምሩክ ኮምሽን ባለሙያ እቃው እንዲወጣ የተፈቀደበት ደብዳቤ በማስመሰልና ሐሰተኛ የደብዳቤ ፎቶ በመጠቀም አስመጪው ሕጋዊ እንደሆነ ተደርጎ የሚሰራጨው መረጃ ሐሰተኛ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታዉቋል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *