የ4ጂ ፈጣን ኢንተርኔት አገልግሎት በህዳሴው ግድብ እና አካባቢው ተጀመረ::
አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2014 የኢትዮ ቴሌኮም ምዕራብ ሪጅኑ የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስ ፈጣን ኢንተርኔት አገልግሎት ዛሬ ህዳሴው ግድብ እና አካባቢው ተጀመረ። የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬሕይወት ታምሩ አገልግቱን ዛሬ በአሶሳ ከተማ ተገኝተው በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት፥ በምዕራብ ሪጅን የሚገኙ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ
አካባቢን ጨምሮ በመተከል ዞን ግልገል በለስ፣ አሶሳ እና ባምባሲ ከተሞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሆነዋል። በአገልግሎቱ ከ108 ሺህ በላይ ደንበኞች ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል። ይህም የአንደኛው ምዕራፍ የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ. አድቫንስ አገልግሎት ማጠናቀቂያ እንደሆነ ጠቁመው 106 ከተሞች ለማዳረስ ታቅዶ በ96 ከተሞች ስኬታማ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል። በተለይም ወደ ምዕራብ ሪጅን የሚደረገውን የአገልግሎቱ ማስፋፊያ ፈታኝ እንደነበር የጠቆሙት ወይዘሮ
ፍሬሕይወት፥በባለድርሻ አካላት የተጠናከረ ድጋፍ ስራው መጠናቀቁን አስታውቀዋል። የሁለተኛው ምዕራፍ ማስፋፊያ ስራም በተጓዳኝ እየተከናወነ መሆኑን ዋና ስራ አስፈጻሚዋ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።