የመንግስት አገልግሎትን ለመስጠት የሚያስችል ኤሌክትሮኒክስ አውታር ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ ነው
የመንግስት አገልግሎትን ለመስጠት የሚያስችል ኤሌክትሮኒክስ አውታር ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ ነው።
ስርዓቱ ዜጎች ባሉበት ቦታ ሆነው መረጃ ለመለዋወጥ፣ የንግድ ስምምነት ለመፈፀም፣ የንግድ ስራዎችን ለመምራት፣ ለመማርና ሌሎች መንግስታዊ ተግባራትን ለማከናወን የሚያስችላቸው ነው ተብሏል፡፡
የመንግስት ኤሌክትሮኒክስ አገልግሎቱ የፌደራል፣ ክልል፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ ወረዳና ቀበሌን በማስተሳሰር ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ቀልጣፋና የማይቆራረጥ አገልግሎት ለመስጠትም የሚያስችል ነው ተብሏል።
አገልግሎቱን ለመጀመር የመሰረተ ልማት ለመግንባት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የፌደራልና የክልል ተቋማት ሃላፊዎች በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ውይይት እያደረጉ መሆኑም ተገልጿል፡፡
ስርዓቱን ለመዘርጋት የበይነ መረብ ተደራሽነትና ዋጋ እንደ ችግር ተነስቷል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ አሁን ላይ ያለውን 40 ጊጋ ባይት የኢትዮጵያ የበይነ መረብ አገልግሎት በሚቀጥሉት አመታት 10ሺ ጊጋ በይት ለማድረስ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡
ይህ ማሻሻያ ቀልጣፋና የማይቆራረጥ የመንግስት አገልግሎትን ለመስጠት ሊዘረጋ ለታሰበው የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት አይነተኛ ሚና ይጫወታል ተብሎ እንደሚታመንም ነው የተገለጸው፡፡