loading
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በትግራይ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀ::

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25፣ 2013 የሚኒስትሮች ምክር ቤት በትግራይ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀ::የኢፌዴሪ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በትግራይ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀ፡፡የኢፌዴሪ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረገው 21ኛ አስቸኳይ ልዩ ስብሰባ መንግሥት የሀገርን ሰላምና ሕልውና፣ የሕዝብንና የዜጎችን ደህንነት የማረጋገጥ እና ሀገሪቷን ወደ ሁከትና ብጥብጥ የሚወስዱ ማናቸውንም ድርጊቶችን የመከላከል ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን በመገንዘብ፤ እንዲሁም በትግራይ ብሔራዊ ክልል ውስጥ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን እንዲሁም የሕዝብን ሰላምና ፀጥታ አደጋ ላይ የሚጥሉ በተለይም የሀገርን ሉዐላዊነት የሚገዳደሩ፣ የፌደራል መንግሥት በሕገ መንግሥቱ የተሰጠውን ሥልጣንና ኃላፊነት በክልሉ እንዳይወጣ እና ሀገሪቷን የጦር አውድማ የሚያደርጉ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔዎችን ጭምር በመጣስ በርካታ ሕገ ወጥ ተግባራት እየተፈፀሙ በመሆኑ፤ ይህን ሁኔታ በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን በመረዳት፤ በሕገ መንግሥቱ በተደነገገው መሠረት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመጠበቅ ልዩ እርምጃዎችን መውሰድ የሚያስችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደንገግ እና ተግባራዊ በማድረግ ሁኔታውን በመቆጣጠር በሀገሪቱ ሰላምና ሕልውና ላይ የተጋረጠውን አደጋ መከላከል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 93/1/ሀ መሰረት የሚከተለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለስድስት ወራት ተፈጻሚ የሚሆን ሲሆን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈፅም በኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሰብሳቢነት የሚመራና አግባብነት ካላቸው አካላት የተውጣጡ አባላት ያሉት ግብረኃይል በዚህ አዋጅ ተቋቁሟል።
ግብረኃይሉ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሆን ‘‘የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግብረሀይል’’ ተብሎ ይጠራል። አዋጁ በመላው የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መስተዳድር ተፈፃሚ የሚደረግ ሲሆን፣ እንደ አስፈላጊነቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተፈፃሚ ወይም ቀሪ የሚሆንባቸውን ተጨማሪ አካባቢዎችን ግብረኃይሉ በሚያወጣው በመመሪያ ይወስናል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አስመልክቶ ዝርዝር መረጃዎች በየጊዜው ለህብረተሰቡ የሚሰጡ ይሆናል።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *