የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ በእስራኤል ኤምባሲዋን ልትከፍት ነው፡፡
አዲስ አበባ፣ነሐሴ 15፣ 2012 የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ በእስራኤል ኤምባሲዋን ልትከፍት ነው፡፡የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንዋር ጋርጋሽ በቪዲዮ ኮንፈረንስ ውይይት ወቅት በቴልአቪቭ ኤምባሲያችንን እንከፍታለን ማለታቸውን አናዶሉ የዜና ወኪል ዘግቧል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ባሳለፍነው ሳምንት ከእስራኤል ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት መፈራረማቸውን አስታውሰው፤ በዓለም አቀፍ መርህ ሁለት ሀገራት ሊኖራቸው በሚገባው ግንኙነት መሰረት አቡዳቢ በቴላቪቭ ኤምባሲዋን ትከፍታለች ብለዋል፡፡ሚኒስትሩ አክለውም በጣም ግልጽ የሆነው ነገር በቴላቪቭ ኤምባሲ ይኖረናል ነው ያሉት፡፡
ከእስራኤል ጋር ባደረግነው ውይይትም በፍልስጤም የሚደረገው የመሬት ወረራ እንዲቆም ከመግባባት ላይ ደረስናል ያሉት ሚኒስትሩ በሁለቱ ወገኖች ያለውን ግጭት ለመፍታትም ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በዌስት ባንክ የሚደረገውን የቤት ግንባታ ለጊዜውም ቢሆን ገታ ለማድረግ የተስማሙ ሲሆን በጉዳዩ ላይ የሚደረገው የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይቱ እንዲቀጥል ይደረጋል ብለዋል፡፡