loading
የአውሮፓ ህብረት ለዩክሬን መሳሪያ ገዝቶ ሊሰጥ መዘጋጀቱን የህብረቱ ፕሬዚዳንት ተናገሩ::

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2014 የአውሮፓ ህብረት ለዩክሬን መሳሪያ ገዝቶ ሊሰጥ መዘጋጀቱን የህብረቱ ፕሬዚዳንት ተናገሩ:: የአውሮፓ ህብረት ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌይን እሁድ አመሻሽ ላይ በሰጡት መግለጫ ለኬቭ ወታደራዊ ድጋፍ ለማድረግ ተስማምተናል ብለዋል፡፡ ይህን የምናደርገው ዩክሬን ራሷን ከሩሲያ ጥቃት እንድትከላከል ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ መሰረታቸውን በህብረቱ አባል ሀገራት ያደረጉ የሩሲያ ሚዲያዎችን ከስርጭት ማገዳቸውንም ገልጸዋል፡፡


ዩክሬናዊያን ሞስኮ የፈጸመችባቸውን ወረራ ለመመከት በጀግንነት ሲዋደቁ ህብረቱ ዝም ብሎ አያይም፤ ከወታደራዊ ድጋፉ ባሻገር በሩሲያ ላይ የተጀመረውን ማእቀብም አጠናክረን እንቀጥላለን ነው ያሉት ቮንደር ሌይን ፡፡ በዚህም የአውሮፓ ህብረት ለመሳሪያና ለተለያዩ ቁሳቁሶች ግዥ የሚሆን ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ
ገንዘብ መመደቡን ዶቸቬሌ ዘግቧል፡፡

ንብረትነታቸው የሩሲያ የሆኑ ወይም በእሷ የሚተዳደሩ አውሮፕላኖችም በህብረቱ ሀገራት ሰማይ እንዳይበሩ የሚያደርግ የክልከላ ሀሳብ መቅረቡንም ፕሬዚዳንቷ ይፋ አድርገዋል፡፡ በዩክሬን ጦርነት የከፈቱት ፕሬዚዳንት ፑቲን በበኩላቸው የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች በተጠንቀቅ እንዲጠብቁ ለመከላከያ ሃይላቸው ትእዛዝ መስጠታቸው ተሰምቷል፡፡ የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ደግሞ ከቤላሩሱ አቻቸው ጋር ባደረጉት የሥልክ ውይይት ከሞስኮ ጋር በሰላም ዙሪያ ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል ነው የተባለው፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *