የአፍሪካ ሃገራት ግብረገብነትን ያበላሻሉ ያሏቸውን ሙዚቃዎች እያገዱ ሙዚቀኞቹንም እየቀጡ ነው
አርትስ 12/03/2011
የአፍሪካ ሙዚቀኞች ለሙዚቃዎቻቸው ቪዲዮ ከማሰራታቸው በፊት ቆም ብለው እንዲያስቡ የሚያደርግ ዘመቻ ተጀምሮባቸዋል። በተጋለጠ አለባበስ መቀረጽ እና ከስነምግባር ባፈነገጠ የሰውነት እንቅስቃሴ መደነስም በአንዳንድ የአፍሪካ ሃገራት ዘብጥያ የሚያወርድ እየሆነ ነው።
ከሰሞኑ የታንዛኒያ የስነምግባር ጠበቆች ሰው ፊት አይቀርብም ያሉትን ወሲባዊ እንቅስቃሴ የበዛበት ሙዚቃ አግደው ሙዚቀኞቹንም 9 ሚሊዮን ሽልንግ ወይም 3ሺህ 930 ዶላር ቀጥተዋል።
የስነምግባር ጠበቆቹ ዳይመንድ ፕላትኑሙዝ እና ራይቫኒ የተባሉ የታንዛኒያ ሙዚቀኞች የተጫወቱትን ምዋንዛ የተባለ ሙዚቃ “ቆሻሻ” ሲሉ አጣጥለውታል።
የሙጉፉሊ መንግስት እስካሁን ድረስ ሞራለ ቢስ ያላቸውን 20 የሙዚቃ ቪዲዮች በየትኛውም መገናኛ ብዙሃን ለእይታ እንዳይቀርቡ አግዷል።
በታንዛኒያ ከሙዚቀኛ ጀሚማህ ካንሲሜ ሙዚቃ በላይ ጩኸት የበዛበት አርቲስት ግን አልተገኘም። በመድረክ ስሟ የወንዶች ህመም ማስታገሻ የምትባለው አርቲስቷ “የኔ እንስሳ” (ኢንሶሎ ያንጌ) በሚል ርዕስ የተጫወተችው ሙዚቃ ለአምስት ሳምንት እስር ዳርጓታል።የሙዚቃ ክሊፑ አርቲስቷ በውስጥ ሱሪ ብቻ የምትታይበት ነው ተብሏል።
ኬንያም ዘመቻውን በመቀላቀል ከሞራልና ስነምግባር ያፈነገጡ ናቸው ያለቻቸውን አራት ሙዚቃዎች በቴሌቪዠን እንዳይተላለፉ አግዳለች።
በሩዋንዳም አለቅጥ ምዕራባዊ ዘይቤ የተከተለ ነው የተባለ ሙዚቃ ለህዝብ እይታ እንዳይቀርብ ተደርጓል።
በተጋለጠ ሰውነት ትደንሳለች ተብላ የምትወቀሰው የደቡብ አፍሪካዊቷ ዳንሰኛ ዞድዋ ዋባንቱ ወደዛምቢያ እንዳትገባ መከልከሏም ታውቋል።
የኢስት አፍሪካን ዘገባ እንደሚለው የአፍሪካ ሃገራት የጀመሩት ተግባር ስህተት አይደለም። ፖለቲከኞች አዲሱ የአፍሪካ ትውልድ እንዴት እንደሚደንስ እና እንደሚዘፍን መቆጣጠር ካቃታቸው የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ እንዴት እንደሚመርጥም መቆጣጠር ያቅታቸዋል ብሏል።