የአፍሪካ ህብረት ሰንደቅ ዓላማ ከኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ጋር አብሮ እንዲውለበለብ የሚደነግገው አዋጅ ለውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመራ::
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2012 አምስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአምስተኛ አመት የስራ ዘመኑ ባካሄደው 13ኛ መደበኛ ስብሰባው ነዉ የአፍሪካ ህብረት ሰንደቅ ዓላማ ከአገራችን ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ጋር አብሮ እንዲውለበለብ የሚደነግገውን ረቂቅ አዋጅ ለውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመራው፡፡ምክር ቤቱ የአፍሪካ ህብረት ሰንደቅ ዓላማ፣ መዝሙር እና የአፍሪካ ቀንን በሚመለከት የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ለዝርዝር እይታ በሙሉ ድምጽ ለቋሚ ኮሚቴው መርቶታል፡፡ረቂቅ አዋጁ የአፍሪካ ቀን ታስቦ እንዲውልና ለህብረቱ ያለንን አጋርነት፣ ቁርጠኝነት እንዲሁም ተደማጭነትና ወንድማማችነት እንዲጎለብት ሚናው የላቀ መሆኑን የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ገልጸዋል ፡፡
የህብረቱ ሰንደቅ ዓላማ ተፈጻሚነት ወሰን የተቀመጠ ሲሆን ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቅጥር ግቢ፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ቅጥር ግቢ ፣ በፕሬዝዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤትና መኖሪያ ቤታቸው ህንጻዎች ላይ፣ በሚኒስቴር እና ለሚኒስቴሩ ተጠሪ በሆኑ ተቋማት ህንጻዎች፣ በኢትዮጵያ በተመዘገቡ ንግድ መርከቦች፣ ጀልባዎችና አውሮፕላኖች ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆን በአዋጁ ላይ ተብራርቷል፡፡
ረቂቅ አዋጁ የአፍሪካ ህብረት በ50ኛው ክብረ-በዓል ወቅት ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት የህብረቱ ሰንደቅ ዓላማ ከአገራችን ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ጋር አብሮ እንዲውለበለብና የህብረቱ መዝሙር ከኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር ጋር ጎን ለጎን ለማዘመር ኢትዮጵያ ውሳኔውን መደገፏን የሚያሳይ እንደሆነ አምባሳደር መስፍን መናገራቸውን ምክርቤቱ አስታውቋል።