loading
የአፍሪካ ህብረት እና ኢኩዋስ የጊኒ የምርጫ ሂደት ችግር እንዳልታየበት ተናገሩ::

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2013 የአፍሪካ ህብረት እና ኢኩዋስ የጊኒ የምርጫ ሂደት ችግር እንዳልታየበት ተናገሩ:: የምእራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ እና አፍሪካ ህብረት የምርጫ ሂደቱን ከታዘቡ በኋላ በሰጡት መግለጫ፤ የጊኒ ህዝብ ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እዲካሄድ ላደረገው ብስለት የተሞላበት እንቅስቀቃሴ አድናቆታቸውን ቸረዋል፡፡
ከተቃዋሚዎቹ በኩል ግን በምርጫው ወቅት የተወሰኑ ችግሮች እንደነበሩ ሲናገሩ ተደምጠዋል ነው የተባለው፡፡ የፕሬዚዳንት አልፋ ኮንዴ ቀንደኛ ተቀናቃኝ ሆነው የቀረቡት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ሴሉ ዲያሎ ደግሞ ምርጫውን አሸንፌያለሁ በማለት ደጋፊዎቻቸውን አስጨፍረዋል፡፡

ሁለቱ ተቋማት የትዝብት ሪፖርታቸውን ባቀረቡበት ወቅት ጊኒ ግልፅነት የታየበት ምርጫ ማካሄዷን በመግለፅ ነገሩ ቀድሞ እንደተፈራው አይደለም የሚል ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን በበኩሉ የተቃዋሚ መሪው የሴሉ ዲያሎ የአሸንፌያለሁ መግለጫ ውጤት ሳይገለፅ የተሰጠ በመሆኑ ወቅቱን ያለጠበቀና ህዝቡን ወደግጭት የሚያመራ ነው በማለት አውግዟል፡፡ዲያሎ ግን የመጀመሪያውን ዙር ምርጫ በጥሩ ውጤት ማሸነፋቸውን በኩራት ነው ለደጋፊዎቻቸው የተናገሩት፤ ደጋፊዎቻቸውም የተባሉትን አምነው በኮናክሪ ጎዳናዎች እየተዘዋወሩ ደስታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *