የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሀገራችን ተቋማትን መገንባትና ለትውልድ ማሸገጋር እንደምትችል ማሳያ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።
አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2014 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሀገራችን ተቋማትን መገንባትና ለትውልድ ማሸገጋር እንደምትችል ማሳያ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የባንኩን የ80ኛ ዓመት የምስረታ ክብረ በዓልና ያስገነባውን ዘመናዊ ህንፃ ማስመረቁን በማስመልከት በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ፅሁፍ ነው፡፡ ባንኩ ያስገነባውን ባለ 53 ወለል ህንፃ በሚያስመርቅበት ወቅት ተገኝተው ባደረጉት ንግግርም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዋርካ ነው” ብለዋል፡፡ ለዚህ አባባላቸውም ባንኩ በኢትዮጵያ ያሉ ሁሉም ባንኮች ካላቸው ተቀማጭ ሃብት ከ52 በመቶ
በላይ የሚሆነውን ድርሻ መያዙን በማሳያነት አንስተዋል፡፡
በተጨማሪ ባንኩ በአገሪቱ በዘርፉ ካለው አጠቃላይ ሃብት ውስጥ ከ62 በመቶ በላይ የሚሆነውን መያዙም የፋይናንስ ዋርካ ያሰኘዋል ነው ያሉት።
አሁን ላይ ከአንድ ትሪሊየን ብር በላይ ሃብት ያለው ባንክ መሆኑም ሌላኛው መገለጫው መሆኑን አንስተዋል። ባንኩ ያስመረቀው ህንጻ 209 ነጥብ 15 ሜትር ከፍታ እና 65 ሺህ ስኩየር ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን በውስጡም እስከ 1 ሺህ 500 መኪና ማቆም የሚያስችል ዘመናዊ ፓርኪንግ፣ የስብሰባ
አዳራሽ፣ ሙዚየም፣ ሲኒማ ቤት እና ሌሎች የአገልግሎት መስጫ ክፍሎች አሉት፡፡
የትናንትን ሳይረሱ ትምሕርት መቅሰማቸውን የሚቀጥሉና ዘመንን የሚዋጁ ተቋማትን መገንባት ያስፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባንኮቻችን ዓለም አቀፍ ተወዳሪ ለመሆን ከሕንጻ ግንባታ ባለፈ በሰው ሀይልና በአሰራር ሊዘምኑ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያስመረቀው ይህ ዘመናዊ ህንፃ ለግንባታው 303 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጎበታል፡፡