የወይብላን ጉዳይ ለማጣረት በግብርኃይል እየተመረመረ ነው- የመንግሥት ኮሙኒኬሽን
አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2014 በጥምቀት በዓል ላይ በቡራዩ ከተማ አስተዳደር ወይብላ ቅድስት ማሪያም ቤተክርስቲያን የተፈጸመውን ድርጊት ግብርኃይል ተቋቁሞ እየመረመረ እንደሚገኝ መንግሥት አስታወቀ፡፡የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጡት መግለጫ ግብርኃይሉ ከፌዴራል ፖሊስ ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ከኦሮሚያ ክልል የተውጣጣ እንደሆነ ገልጸው ውጤቱ ሲደርስ ለሕዝብ ይፋ ይሆናል ብለዋል፡፡
ሌሎች የጸጥታ ችግር በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ኃይማኖታዊ በዓሉ በሰላም መከበሩንም አስታውሰዋል፡፡ በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ከተማ የተካሄደው ታላቁ ሩጫ በሰላም መጠናቀቁንም ገልጸዋል፡፡ በዓላቱ በሰላም ተከብረው መጠናቀቃቸው የአንዳንድ ሰላም ጠል ኃይሎች ሴራ መክሸፉን እንደሚያሳይም ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ አመላክተዋል፡፡ በቅርቡ በአዲስ አበባ የሚካሄደው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ እየተሰራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡