የዓለም ጤና ድርጅት አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ባለፈው ሳምንት በ16 በመቶ ቀንሶ መታየቱን ገለፀ፡፡
አዲስ አበባ፣የካቲት 10፣ 2013 የዓለም ጤና ድርጅት አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ባለፈው ሳምንት በ16 በመቶ ቀንሶ መታየቱን ገለፀ፡፡ ድርጅቱ ማክሰኞ አመሻሽ ላይ ባወጣው ሪፖርት ከኮቪድ 19 ጋር የተያያዘ የሞት መጠን መቀነሱንም አስታውሷል፡፡ ድርጅቱ ከስድስት የቁጥጥር ቀጠናዎች ከተላኩለት የበሽታው ስርጭት ሪፖርቶች መካከል በአምስቱ አዲሱ ቫይረስ በሁለት አሃዝ መቀነስ ሲያሳይ በሜዲትራኒያን አካባቢ ብቻ በ7 በመቶ ጭማሪ
መመዝገቡ ታውቋል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ከዚሁ ጋር አያይዞ ይፋ ባደረገው መረጃ በኮሮናቫይረስ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በ10 በመቶ መቀነሱንም ተናግሯል፡፡ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድኃኖም ቀላል የሚባሉትን የህዝብ ጤና አጠባበቅ ስራዎችን በመስራት ብዙ አደጋ መቀነስ እንደሚቻል በግልፅ የሚያሳይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በዚሁ በተገባደደው ሳምንት የበሽታው ስርጭት በአፍሪካና በምእራባዊ ፓስፊክ በ20 በመቶ፣ በአውሮፓ 18 በመቶ፣ እንዲሁም በደቡብና ሰሜን አሜሪካ በ16 በመቶና በደቡብ ምስራቅ እስያ በ13 በመቶ ቀንሷል ብሏል ድርጅቱ፡፡ ሆኖም እንዲህ አይነት ሪፖርቶች ተስፋን የሚፈነጥቁ ቢሆንም በሌላ መልኩ ደግሞ በህዝቡ ዘንድ መዘናጋትን ስለሚፈጥሩ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ባለሞያዎች ይመክራሉ፡፡