የግብፅ የፀጥታ ሃይሎችና የ”አይ ኤስ አይ ኤል” ግብግብ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2014 በሲናይ በርሃ ለተገደሉት የግብፅ ወታደሮች አይ ኤስ አይ ኤል ሃላፊነቱን እደሚወስድ ገለጸ፡፡ ቡድኑ ባለፈው ቅዳሜ እለት በሲናይ በርሃ 11 የግብፅ ወታደሮችን መግደሉንና መሳሪያቸውን መማረኩን ነው ይፋ ያደረገው፡፡ ጥቃቱ የተፈጸመው ከስዊዝ ካናል በስተምስራቅ በምትገኘው ኢማኢሊያ ከተማ መሆኑን አልጀዚራ በዘገባው አስነብቧል፡፡
አይ ኤስ አይ ኤል በሲናይ ባህረ ገብ በኬላ ጥበቃ ላይ በነበሩ ግብፃዊያን ላይ ተኩስ ከፍቶ ድል እንደቀናው ቢናገርም የግብፅ ወታዳራዊ ሃይል በበኩሉ ጥቃት አደራሾቹን እያሳደዳቸው መሆኑን ገልጿል፡፡ እንደ አወሮፓዊያኑ አቆጣጠር ከ2013 ሟቹ ፕሬዚዳንት በመፈንቅለ መንግስት ከተወገዱ ወዲህ አካባቢው በግጭት ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ከሁለቱም ወገን በርካቶች ህይወታቸውን ማጣታቸው ይነገራል፡፡
ይህን ተከትሎም የግብጽ መንግስት ከፌብሯሪ 2018 ጀምሮ በሲናይ በርሃ፣ በናይል ዴልታና ሀገሪቱ ከሊቢያ በምትዋሰንበት አካባቢ ሰፊ ፀረ ሽብር ዘመቻ እያደረገ ይገኛል፡፡ ፕሬዚዳንት አብደልፈታህ አልሲሲ በቀጠናው ያለው ሁኔታ ሀገራችን ሽብርንና ሽብርተኞችን ለማጥፋት ያላትን ቁርጠኝነት ለአፍታም አይሸረሽረውም ብለዋል፡፡ የአፍሪካ ህብረት፣ አሜሪካና ፈረንሳይ ሰሞኑን በግብጽ ወታደሮች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ያወገዙ ሲሆን በተለይ ዋሽንግተን ለካይሮ ሀዘኗን መግለጿን ነው የተሰማው፡፡