loading
የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ ጭፍጨፋ የፈፀመበት 84ኛው የሠማዕታት ቀን ታስቦ ዋለ::

አዲስ አበባ፣የካቲት 12፣ 2013 የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ ጭፍጨፋ የፈፀመበት 84ኛው የሠማዕታት ቀን ታስቦ ዋለ:: በአድዋ ሽንፈትን የተከናነበው የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር የዛሬ 84 ዓመት ዳግም ኢትዮጵያን ሲወር በአራቱም አቅጣጫ ይፋለሙት በነበሩ ኢትዮጵያዊያ ላይ ግፍና በደል ፈጽሟል። ግፍና በደሉን አንቀበልም ያሉት አብርሃም ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ግራዚያኒን በቦምብ ለመግደል ያደረጉትን ያልተሳካ ሙከራ ተከትሎም የግራዚያኒ ጦር የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም በኢትዮጵያዊን በተለይም በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ ዘግናኝ ጭፍጨፋ አድርሷል።

ዕለቱን ለማሰብ ምክትል ከንቲባ አዳነች አበቤ፣ የጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኀበር ተወካይ ስድስት ኪሎ በሚገኘው የሰማዕታት ሐውልት ስር የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል። በዛሬው 84ኛ ዓመት የሰማዕታት መታሰቢያ ደማቸውን ለሃገር ክብር ላፈሰሱ፣ አጥንታቸውንም ለሕዝብ ነጻነት ለከሰከሱ ጀግኖች ሰማዕታት ክብር እንሰጣለን ብለዋል ምክትል ከንቲባዋ።

ከምንም በላይ ሰማዕታትን የምናከብረው አንድነታችንን አጠንክረን፣ አብሮነታችንንም አጎልብተን የጀግንነት ተግባር በመፈጸም አገራችንን የብዙ ድልና የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ ነው ሲሉ ተናግረዋል። በሰማዕታት መታሰቢያ ስነ ስርዓቱ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና የጀግኖች አርበኞች ቤተሰቦች
ታድመዋል፤ የአበባ ጉንጉንም አስቀምጠዋል።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *