ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ ቀጣዩ ምርጫ በፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ይካሄዳል አሉ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ ቀጣዩ ምርጫ በፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ይካሄዳል አሉ
አርትስ 13/03/2011
ዛሬ በተካሄደው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 7ኛ መደበኛ ስብሰባ ወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ በመሆን ተመርጠዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ ወ/ሪት ብርቱካንን በዕጩነት ሲያቀርቡ ቀጣዩ ብሔራዊ ምርጫ ፍትሐዊ በሆነ ዴሞክራሲያዊ መንገድ እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡ የሚቀጥለው ምርጫም አይጭበረበርም ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡ ከዚህ በፊት የተደረጉ ምርጫዎች ለመሪ ፓርቲው ያደላሉ ይባሉ የነበሩ ሲሆን አሁን ይህን ለማስቀረት ነፃ የሆነ ምርጫ ቦርድ አመራር በአዲስ ማቋቋም በማስፈለጉ ለቦርዱ ሰብሳቢነት በዕጩነት ወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳን ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡ ወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ለህግና ስርዓት መከበር ፅኑ እምነት ያላቸው፣ መስዋዕትነት መክፈል የሚችሉ፤ ነፃ የሆኑ፣ ህግን የሚያውቁ፣ የማይፈሩ፣ ለፍትህ ጠበቃ የቆሙ ናቸው ብለዋል ጠ/ሚኒስትር አቢይ፡፡ በተጨማሪም ከዚህ በፊት ሀገር ቤትና ባህር ማዶ በኃላፊነት ባገለገሉባቸው ተቋማት ምስጉን ፣ በዘርፉ አንቱ የተባሉና ያስመሰከሩ፤ በኢህአዴግ ላይ የሚነሳውን ቅሬታ የሚቀርፉ በመሆናቸውና ላለፉት ዓመታት በማንኛውም ፓርቲ ውስጥ ገለልተኛ የነበሩ፤ ስለእርሳቸው ምስክርነት የተጠየቁ በሙሉ ድምፅ የተደገፉ በመሆናቸውና ነፃ ሆነው ለማገልገል ፈቃደኝነታቸውን በማሳየታቸው ምክር ቤቱ እንዲያፀድቅላቸው አቅርበዋል፡፡ የምክር ቤቱ አባላትም በዕጩ ሰብሳቢዋ ላይ የድጋፍ ሀሳብ የሰጡ ሲሆን ከፓርቲ ገለልተኝነታቸው ጋር በተያያዘ ጥያቄ አንስተዋል ይህም መረጋገጡን ጠ/ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡ ወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ በአብላጫ ድምፅ በመመረጥ፤ የተጣለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ቃለ መሀላ ፈፅመዋል፡፡ የቦርድ አባላት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር በሰብሳቢዋ አማካኝነት የሚቀርቡ ይሆናል ተብሏል፡፡