ለላልይበላ ቅርስ መጠገኛ የሚሰባሰበው ገንዘብ 50 ሚሊዮን ብር ደረሰ
አርትስ 12/02/2011
‹‹ላልይበላ በገንዘብ የሚተመን አይደለም፤ በዚህ ጉዳይ ስንገፋፋ ቅርሱን አደጋ ላይ መጣል የለብንም›› ሲሉ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊአቶ ልዑል ዮሐንስ ተናገሩ፡፡ የክልሉ መንግሥት ይህን በመረዳት ከላልይበላ በላይ የሚያሳስበው ጉዳይ እንደሌለም ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል የሚገኙ ቅርሶች ‹‹በአንድ ዘመን የነበሩ ስልጣኔዎች በመሆናቸው እርጅናቸው ደግሞ በዚህ ዘመን ሆኗል፡፡ ይህ ለክልሉ መንግሥትና ሕዝብ ከባድ ፈተና ነው፡፡ ይሁን እንጂችግሩ የባሰበትን በማየት ሳይንሳዊ ጥገና እንዲደረግ ጥናቶች ተጠናቀዋል›› ብለዋል አቶ ልዑል፡፡ የክልሉ መንግሥት በየዓመቱ የሚቀጥል 30 ሚሊዮን ብር መፍቀዱንም አስታውቀዋል፡፡
እስካሁን ከቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን 20 ሚሊዮን እና ከአማራ ክልል መንግሥት 30 ሚሊዮን ብር በድምሩ 50 ሚሊየን ብር ለጥገናው ዝግጁ ሆኗል፡፡
‹‹የፌዴራል መንግሥትን ድጋፍ እየተጠባበቅን ነው፤ አሁንም ግን ሙሉ ጥገናውን ለማድረግ 300 ሚሊዮን ብር የሚያስፈልግ በመሆኑ ኅብረተሰቡ ቅርሱ አደጋ ላይ መሆኑ እንዳሳሰበውሁሉ ለደኅንነቱም በገንዘብ እና በሀገር በቀል ዕውቀቶች ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፋለሁ›› ብለዋል ምክትል ቢሮ ኃላፊው፡፡
አቶ ልዑል ዮሐንስ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ‹‹ቅርሱን ለመጠገን የሚያስፈልጉ ቴክኖሎጂዎች ተቀባይነት በማግኘታቸው ገንዘብ ወደ ማሰባሰቡ ገብተናል›› ብለዋል፡፡
የላልይበላ ቅርስን ለመጠገን በአዋጅ በተቋቋመው የገንዘብ ማሰባሰብያ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ‹‹የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት›› በሚል ስም በሒሳብ ቁጥር 1000227933357›› ዜጎች የቻሉትን ገቢ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በባንኩ የገባው ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ለላልይበላ ቅርስ መጠገኛ እንዲውልም የጋራ ውሳኔ ላይ መደረሱንም አቶ ልዑል ዮሐንስገልፀዋል፡፡
አብመድ