ሱዳን በቀይ ባህር አካባቢ ሩሲያ የጦር ሰፈር እንድታቋቁም መፍቀዷ ግብፅን ቅር አሰኝቷል ተባለ፡፡
አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2014 ሱዳን በቀይ ባህር አካባቢ ሩሲያ የጦር ሰፈር እንድታቋቁም መፍቀዷ ግብፅን ቅር አሰኝቷል ተባለ፡፡ የሱዳንን ሉዓላዊ ምክር ቤትን በምክትልነት የሚመሩት ጄኔራል ሞሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ ሞስኮ ደርሰው በተመለሱ ማግስት ሀገራቸው ለሩሲያ የጦር ሰፈር ግንባታ መፍቀዷን ይፋ አድርገዋል፡፡
ዳጋሎ በመግለጫቸው ይህን በማድረጋችን ብሔራዊ ጥቅማችን እስካልተነካ ድረስ ስህተት የለውም የሚፈጥረው የፀጥታ ስጋትም የለም ብለዋል፡፡
የግብጽ ባለስልጣናት ግን የካርቱም እንቅስቃሴ ለቀጠናው ሰላምና ፀጥታ ስጋት ነው በማለት ቅሬታቸውን መግለጸቸውን አል አረቢ አልጀዲድ አስነብቧል፡፡
በሩሲያ የ8 ቀናት ጉብኝት አድርገው የተመለሱት ዳጋሎ ከሩሲያም ሆነ ከሌሎች ሀገራት ጋር በዚህ መልኩ በትብብር መስራት የተለመደ በመሆኑ የሚያስደንቅ ነገር የለም ነው ያሉት፡፡ ካይሮ ግን ጎረቤቷ ካርቱም በቀይ ባህር ዳርቻ በምትገኘው ፖርት ሱዳን ለሞስኮ የጦር ሰፈር ግንባታ ስለፈቀደችበት አግባብ ማብራሪያ እንደምትፈልግ መናገሯ ተሰምቷል፡፡
ሱዳን በዚህ መልክ ወደ ሩሲያ ፊቷን ያዞረችው ባለፈው የተካሄደውን መፈንቅለ መንግስት ተከትሎ ምእራባዊያን ኢኮኖሚያዊ ድጋፋቸውን ስላቋረጡባት አማራጭ ፍለጋ ነው ተብሏል፡፡ ሩሲያ በሌሎች ሀገራትም የጦር ሰፈር እንዳላት የተናገሩት ዳጋሎ የሌሎቹን ፍላጎት ባናውቅም እኛ ግን በሁሉም መስክ ከሞስኮ ጋር በትብብር ከመስራት የዘለለ ድብቅ አላማ የለንም ብለዋል፡፡