loading
የአንጋፋው ማሲንቆ ተጫዋች ለገሰ አብዲ ስርዓተ ቀብር ተፈፀመ

አርትስ 12/02/2011

አርቲስት ለገሰ አብዲ በ1931 በሰላሌ ያያ ቀጨማ ከአባታቸው ከአቶ አብዲ ዳዲ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ፎሌ ጉደታ ተወለዱ፡፡

ለወላጆቻቸው ብቸኛ ልጅ ሲሆኑ፤በልጅነታቸው የአባታቸው ጓደኛ የሆኑትን እውቅ የማሲንቆ ተጫዋች ወሰኑ ዲዶ ን በመከተል በመሲንቆ  ፍቅር እንደወደቁ በአንድ ወቅት ተናግረው ነበር፡፡ ልምምዳቸውን ከሳቸው ጋር ቀጥለው በተወለዱ በ20 ዓመታቸው ከወሰኑ ዲዶ ጋር ወደ አዲስ አበባ መጥተው በሃገር ፍቅር ቴአትር በሙያው መስራት ጀምረው ነበር፡፡

አርቲስቱ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ሀገር ፍቅርን ጨምሮ በብሄራዊ ቴአትር፡ በአዲስ አበባ ቴአትር ማዕከል፤በፖሊስ ኦረኬስትራና በክቡር ዘበኛ የሙዚቃ ስራቸውን አቅርበዋል፡፡

በአፋን ኦሮሞ በነፃነት መዝፈንም ሆነ ሃሳብን መግለፅ በማይቻልበት ወቅት፤ ችግሮችን በማለፍ በመዝፈን ለቋንቋው እድገትና ዕውቅና ታላቅ ተጋድሎን ካደረጉ አንጋፋ የመድረክ ፈርጦች መሃከል እንደሆኑም ይነገርላቸዋል፡፡ በነዚህ ስራዎቻቸውም ከማህበረሰቡ ታላቅ ፍቅርና አክብሮትን አግኝተዋል፡፡

በመድረክ በተለያየ ጊዜ ካቀረቧቸው ዘፈኖች በተጨማሪ 11 የዘፈን ሲዲዎችንና 1 ቪሲዲ አሳትመው  ለገበያ አቅርበዋል

ምንም አይነት ዘመናዊ የሙዚቃ ትምህርትን ሳይማሩ አራቱንም የሙዚቃ ቅኝቶች እንደሚጫወቱ የሚነገርላቸው አርቲሰት ለገሰ አብዲ  ከ 60 ዓመታት በላይ  በሙዚቃው ህይወት ቆይተዋል፡፡

በሃገሪቱ የሙዚቃ አዋቂዎች አድናቆትንም አትርፈዋል፡፡  ከባለቤታቸው ከወ/ሮ እጂጌ አበበ  ጋር ትዳር መስርተው 7 ልጆችን አፍርተዋል፡፡ ስርዓተ ቀብራቸውም  በተወለዱ በ80 ዓመታቸው በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ዛሬ ተፈፅሟል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *