loading
የአፍሪካ ሕብረት 40ኛው የስራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ጉባኤ የሕብረቱ አባል ሀገራት ሚኒስትሮችና የአህጉሩ ልዩ ልዩ ተቋማት ሃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ ተጀምሯል፡፡

አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2014 የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሃማት በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር
በአህጉሩ በየአቅጣጫው እያጋጠመ ያለውን የሰላም እና ፀጥታ ችግር ለመፍታት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ
መስራት ይገባል ብለዋል፡፡


ሊቀመንበሩ የኮሮና ቫይረስ የፈጠረው ተፅዕኖ እና ለመቋቋም ስለሚደረጉ ጥረቶች፣ የአጀንዳ 2063
የአፈጻጸም ሂደት፣ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና እና ሌሎች አህጉራዊ አጀንዳዎችንም አንስተዋል።
የምክር ቤቱ ስብሰባ “የአፍሪካ አህጉርን የስርዓተ ምግብ አቅም መገንባት፣ የሰው ሃብት ልማት፣
የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማትን ማፋጠን” በሚል መሪ ሀሳብ ይመክራል፡፡


ጥር 28 እና 29 ቀን 2014 ዓ.ም ለሚካሄደው 35ኛው የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ የሚቀርቡ
ረቂቅ አጀንዳዎች ላይም ይወያያል ተብሎ ይጠበቃል።
በ40ኛው የስራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ የምስራቅና ደቡብዊ አፍሪካ አገራት
የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ዋና ጸሀፊን ጨምሮ የህብረቱ አባል ሀገራት ሚኒስትሮችና ሚኒስትር ዴኤታዎች
አዲስ አበባ ገብተዋል።


የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት በሕብረቱ አባል አገራት የጋራ ፍላጎት የሆኑ የፖሊሲ
ጉዳዮችን የሚያስተባብርና ውሳኔ የሚሰጥ ነው።
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን አባላትን በመምረጥ የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ እንዲያጸድቅ የሚያደርግ
ሲሆን ከቀጠናዊ የኢኮኖሚ ማህበረሰቦች፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክ፣ ሌሎች የአፍሪካ ተቋማትና
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢኮኖሚ ኮሚሽን ያለው ትብብርና ትስስር እንዲጠናከር የማስተዋወቅ
ስራ ያከናውናል።
የአፍሪካ ሕብረትና የአፍሪካ አጋሮች ያላቸውን ትብብር ማጠናከር የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን በማዘጋጀት
በአህጉሪቷ የሰላም፣ ጸጥታና ሌሎች የጋራ አጀንዳዎች ረቂቅ የውሳኔ ሃሳቦችን ያቀርባል።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *