በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ በእንስሳት ላይ ያደረሰው ጉዳት ወደ ሰው እንዳይሸጋገር እየተሰራ ነው ተባለ፡፡
አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2014 የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ከአጋር አካላት ጋር በመሆን
ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጿል፡፡ ሚኒስትር ዴኤታዋ ሰላማዊት ካሳ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ በሶማሌ ክልል 9 ዞኖች
በተከሰተው የድርቅ አደጋ 960 ሺህ በላይ ዜጎች ተጎጂ በመሆናቸው የእለት ደራሽ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በአጠቃላይ በክልሉ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሰዎች የእለት ደራሽ ድጋፍ ይፈልጋሉ ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ
በዚህም እስከ ታኅሣሥ ወር ድረስ 558 ሺህ ኩንታል እህል በማሰራጨት 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሰዎችን
ማዳረስ እንደተቻለ ጠቁመዋል፡፡
በድጋፉ የዓለም ዐቀፍ የምግብ ፕሮግራምን ጨምሮ ሌሎች አጋር አካላት ተሳትፈውበታል ነው ያሉት፡፡
በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ከ166 ሺህ በላይ ሰዎች በድርቁ ተጎጂ መሆናቸው የተገለጸ
ሲሆን ከዚህ በፊት ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው ጋር ሲደመር 426 ሺህ ደርሷል ነው የተባለው፡፡
በምስራቅ ባሌ እንዲሁም በደቡብ ኦሞ ዞን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖችም እርዳታ ለማሰራጨት እየተሰራ
መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ አክለዋል፡፡
በሌላ በኩል ወደ ትግራይ ክልል የሚገቡ የሰብኣዊ ድጋፎች ከ50 አጋር ዓለም ዐቀፍ ተቋማት ጋር
በመሆን ተጠናክሮ መቀጠሉንም አስታውቀዋል፡፡
በዚህም የአየር ትራንስፖርትን በማመቻቸት መድኃኒቶችና የእለት ደራሽ ምግቦች እየደረሱ ነው
ብለዋል፡፡