loading
የሰብአዊ እርዳታ ከፍ እንዲል ካልተደረገ በትግራይ ከባድ የረሃብ አደጋ ሊከሰት ይችላል::

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 19፣ 2013 የሰብአዊ እርዳታ ከፍ እንዲል ካልተደረገ በትግራይ ከባድ የረሃብ አደጋ ሊከሰት ይችላል:: በትግራይ ረሃብ ሊከሰት እንደሚችል ዩናይትድ ኪንግደምና የተባበሩት መንግሥታት ስጋታቸውን ገለጹ ::በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ በወራት ጊዜ ውስጥ የረሃብ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል የዩናይትድ ኪንግደም ረሃብ የመከላከል ልዩ መልዕከተኛ የሆኑት ኒክ ዳየር አስጠንቅቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ጥረት ከፍ እንዲል ካልተደረገ በትግራይ ክልል ውስጥ ከባድ የረሃብ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮችና የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ባለሥልጣን ማርክ ሎውኮክ መናገራቸዉን ኤኤፍፒን ጠቅሶ ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል፡፡
ሎውኮክ ለጸጥታው ምክር ቤት እንደተናገሩት በትግራይ ክልል 90 በመቶ ምርት ታጥቷል እንዲሁም 80 በመቶ የቀንድ ከብት ተዘርፈዋል ወይም ታርደዋል። በዚህም ሳቢያ በክልሉ ካሉ አምስት ሰዎች መካከል አንዱ ለምግብ ችግር ተጋልጧል ብለዋል።

ባለሥልጣኑ ጨምረውም የተጠናከረ እርምጃ መውሰድ ካልተቻለ አሁን ያለው ሁኔታ የበለጠ እየተባባሰ ይሄዳል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።የዩናይትድ ኪንግደም ልዑኩ ኒክ ዳር በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው በግጭት በተጎዳው የትግራይ ክልል ካደረጉት ጉብኝትና ግምገማ በመነሳት ነው ስጋታቸውን የገለጹት። አሳሳቢ ግድያዎችና የመድፈር ድርጊቶችን የሚያመለክቱ ሪፖርቶችን በመጥቀስ ያለው ሁኔታ አደገኛ ነው ሲሉ ልዩ መልዕክተኛው ገልጸዋል።

ኒክ ዳየር ጨምረውም የግብርና መገልገያዎች፣ የሰብል ዘር እንዲሁም መንደሮች መውደማቸውን በመግለጽ ያለውን ችግር አመልክተዋል። በተዘጉ መንገዶችና በውጊያዎች ምክንያት በክልሉ ከፍተኛ መጠን ያለው ሕዝብ ለመድረስ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝም ተናግረዋል። በተጨማሪም ከጥቂቶች በስተቀር በክልሉ ውስጥ በርካታ የጤና ማዕከላት መውደማቸው አሳሳቢው ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ የጤና ችግር እንደ ረሃብ አደጋው ሁሉ ከፍ ያለ ስጋትን ይደቅናል ብለዋል።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *