መንግስት ባወጣው የምህረት አዋጅ ተጠቃሚ ለመሆን ከታራሚዎች ምን ይጠበቃል?
መንግስት ያወጣው የምህረት አዋጅ ከወጣበት ሐምሌ13ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ተፈጻሚ ይሆናል ተብሏል፡፡
የምህረት አሰጣጡ ለሚቀጥሉት 6 ወራት ስራ ላይ የሚውል ሲሆን፤ የምህረቱ ተጠቃሚ የሚሆኑ ታራሚዎች የተጠየቁበት ወንጀል እስከ ግንቦት 30 የተፈጸመ ከሆነ ብቻ ነዉ ተብሏል፡፡
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በእነዚህ 6 ወራት ውስጥ የምህረቱ ተጠቃሚ ለመሆን ታራሚዎች በአካል በመገኘት ፣ ሰው በመወከል ወይም በፖስታ እና ስልክ ለፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የምህረት እና ይቅርታ ጽህፈት ቤት፣በክልል ፍትህ ቢሮዎች ሪፖርት ማድረግ እና መመዝገብ አልያም ወደ www.fag.gov.et ድረ-ገጽ በመግባት የሚጠየቁትን መረጃዎች በመሙላት መመዝገብ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
ምዝገባውን አለማድረግ ምህረቱን አለመቀበል ተደርጎ ስለሚወሰድ በአዋጁ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ያደርጋል ፡፡ምህረት የተደረገለት ታራሚም የማረጋገጫ ሰርተፊኬት እንደሚሰጠው ተነግሯል፡፡