loading
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ነገ የሚከበረውን የኢሬቻ በዓልን ምክንያት በማድረግ የመልካም ምኞት መልዕክት አስትላለፉ

አርትስ 19/01/2011

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ነገ የሚከበረውን የኢሬቻ በዓልን ምክንያት በማድረግ የመልካም ምኞት መልዕክት አስትላለፉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት ምልዕክትም ኢሬቻ የገዳ ስርዓት መገለጫ እንደመሆኑ ሰላምና ፍቅር የሚንፀባረቅበት የምስጋና ቀን ነው ብለዋል።

ለኦሮሞ ህዝብም ይህ ቀን ልዩ መሆኑን ነው ያነሱት።

የክረምቱ ማለፍን ተከትሎ የሚከበረው የመልካ ኢሬቻ በዓል የተራራቁ ዘመዳሞች የሚገናኙበት፣ የተዘራው ሰብል ፍሬ የሚያፈራበት እንደመሆኑ ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል ብለዋል።

በበዓሉ አብሮ የመኖር እና የመደጋገፍ ባህል ይንፀባረቃል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ አንድ ቋንቋ አናግሮ በፍቅር እና በአንድነት የሚያስተሳስርም እንደሆነ አስታውቀዋል።

ከህፃናት ጀምሮ ወጣቶች በገዳ ስርዓት እንደየእርከኖቹ ኃላፊነትን በመወጣት ከታላላቆቻቸው ልምድ እንደሚቀስሙ በማንሳት፥ ይህም በስርዓቱ ውስጥ ያለውን የዴሞክራሲ ባህል ለማጎልበት የኢሬቻ በዓልም የራሱ ሚና እንዳለው ተናግርዋል።

ገዳ ዘመናዊ የአስተዳደር እርከንን እና የዴሞክራሲ ስርዓትን አቅፎ ስልጣን በማስተላለፍ የሰላም ምንጭ ሆኖም ይቀጥላል ነው ያሉት።

በበዓሉ ላይም እርጥብ ሳር ይዘን ፈጣሪን ስናመሰግን ከመከፋፈል እና ከሀሜት ወጥተን ለአንድነት መለመን ይኖርብናል ብለዋል።

እንደመራለን ስንል ተጨፍልቀን አንድ ዓይነት እንሆናለን ሳይሆን፥ ለልዩነታችን እውቅናና አክብሮት ሰጥተን ተደጋግፈን አብረን እንኖራለን ማለት ነው ብለዋል።

ጥላቻና መቃቃርን አስቀርተን በፍቅርና በመተሳሰብ ሀገራችንን ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ መረባረብ እንደሚገባ ተናግረዋል።

አንዳችን አንዳችንን ማድመጡ የተጀመረውን ለውጥ ለማሻገር እና የተገኙ ድሎችንም ለማስጠበቅ ይረዳል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የዘንድሮ ኢሬቻ አንድነታችንን የምናጠናክርበትና አባገዳዎችን የምንሰማበት እንዲሆን መልካም ምኞቴ ነው ብለዋል።

የተጀመረውን ለውጥ እና አንድነት ለማስቀጠል የኦሮሞ ህዝብም ከሌሎች ህዝቦች ጋር በመተባበር መስራት ይገባዋልም ሱሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሳስበዋል።

በሀገሪቱ የፖለቲካ ባህል ሆኖ የቆየውን መገዳደል፣ መጠላላት፣ አንዱ ሌላውን ማውገዝ፣ መጠላለፍ እና መገዳደል ትተን ወደ መመራረቅ እና መደማመጥ እንድንመጣም ምኞቴ ነው ብለዋል በመልዕክታቸው።

የፖለቲካ አመለካከት ልዩነቶች ቢኖሩም፥ በመወያየት እና በመነገጋር ችግሮችን መፍታት እንደሚቻል ዶክተር አብይ አህመድ ገልፀዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተጀመረው ለውጥ ተጠቃሚ ለመሆን አንድነትን፣ ሰላምን፣ የህግ የበላይነትን ማክበር እና ማስከበር እንዲሁም የፌደራል ስርዓቱን ማጠናከር እና የዴሞክራሲ ስርዓቱን ማስፋት ይገባል፤ ለዚህም ሁሉም የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል ብለዋል።

ኦሮሞ እርስ በራስ ከመጠራጠር እና አንዱ ሌላውን ከማጥቃት ወጥቶ እየተደማመጠ አንድነቱን እንዲያጠናክርም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

መጣላታችንን የሚፈልጉ እኛ የምንከፍትላቸውን ቀዳዳ እንዳይጠቀሙ በጥንቃቄ ልንራመድም ይግባል ነው ያሉት።

የገዳ ስርዓት ኢሬቻ  የፍቅር፣ የሰላም፣ የአንድነት እና የምስጋና እንደመሆኑ መጠን እርስ በርሳችን እየተሳሰብን እና እየተመራረቅን የተሻለ ስራ ለመስራት ቃላችንን የምናድስበት በፍቅር ታድሰን ጥላቻን የምንረታበት እንዲሆንልን እመኛለሁ ብለዋል በመልዕክታቸው።

ኤፍ.ቢ.ሲ

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *