SportSports

የቀያዮቹ የሶስት አስርት ዓመታት ናፍቆት እውንነት የብዙዎቹ ፈንጠዝያ ሆኗል::

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2012 የቀያዮቹ የሶስት አስርት ዓመታት ናፍቆት እውንነት የብዙዎቹ ፈንጠዝያ ሆኗል::
የሰሜን ምዕራብ እንግሊዝ የወደብ ከተማ እንዲሁም የትጉ ሰራተኞች መገኛ እና የንግድ ማእከል
እንዲሁም የሙዚቃ ወዳጅ የሞላባት የሊቨርፑል ከተማ የበረታ ደስታ ውስጥ ትገኛለች፡፡ የቀያዮቹ ወዳጆች
ደግሞ የኮሮና ቫይረስ ትልቅ ስጋት እያንዣበበም ትልቅ ፈንጠዚያ እና የደስታ ስካር ውስጥ ናቸው፡፡
የዚህ ሁሉ ምክንያት ደግሞ በከተማዋ ስያሜ የሚጠራው ታላቁ እግር ኳስ ክለብ ከ30 ዓመታት የተስፋ
ጉዞ በኋላ የሀገሪቱን ዋና ሊግ/ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫ እውን ማድረጉ ነው፤ ትናንት ምሽት ቼልሲ
በተጋጣሚው ማ/ሲቲ ላይ የ2 ለ 1 ድል ከተጎናፀፈ በኋላ፤ የቀያዮቹ የሊጉ ሻምፒዮንነት እንዲታወጅ
ሆኗል፡፡ሊቨርፑል ግንቦት 1/1990 የቀድሞውን የሊግ ዋንጫ ካሳካ በኋላ፤ በአውሮፓ እና በዓለም ጭምር
ቢነግስም አዲሱን የሊግ ቅርፅ ክብር ለመቀዳጀት ሶስት አስርት ዓመታት ታግሏል፡፡ በመጨረሻ ግን ቀያዮቹ
የርሃባቸውን ጊዜ በመቋጨት አንፊልድ ጮቤ እንዲረገግጥ ሆኗል፡፡

ሊቨርፑል እዚህ ክብር ለመድረስ በርካታ አሰልጣኞችን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተጫዋቾች አምጥቷል፤
በቢሊዬን ፓውንድ የሚቆጠር ገንዘብ ፈሰስ አድርጓል፡፡ በውስን ዓመታት የክብሩን መጠን ከ18 ለማሰለፍ
ተቃርቦ ህልሙ ወደ ቅዤት ተቀይሯል፡፡ እነሆ ዘንድሮ ደግሞ በፍልቅልቁ እና በፈላስፋው ጀርመናዊ
አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ እየተመራ የዋንጫ መጠኑን 19 አድርጎ መዝግቧል፡፡ የዚህ መልካም እግር ኳስ
ተግባሪዎች እና ዓመቱን ሙሉ ስኬታማ ጊዜ ያሳለፈው ስብስብ ልባምነት ደግሞ ቦታው ላቅ ያለ ነው፡፡
ሊቨርፑል የዋንጫ መጠኑን 19 ለማድረግ ከ1990/91 የውድድር ዓመት ጀምሮ 1149 ያህል
ጨዋታዎችን፣ የባከነ ክፍለ ጊዜን ሳይጨምር 103 ሺ 410 ደቂቃዎችን በሜዳ ላይ አሳልፏል፡፡
ከእነዚህ ውስጥ ቡድኑ 52 በመቶ በሆነ የማሸነፍ ስሌት፤ በ595 ያህል ጨዋታዎች ሙሉ ሶስት ነጥብ
ሲያሳካ፤ 1968 ጎሎችን በተቃራኒ መረብ ላይ በማሳረፍ 2075 ነጥቦችን መሰብሰብ ችሏል፡፡
ከእነዚህ የቁጥር ጋጋታዎች ውስጥ ግን የዘንድሮዎቹ የ28 ሳምንታት ጨዋታዎች ላይ ድል እና 70 ጎሎች
በአጠቃላይ 86 ነጥቦች የተናፈቀው ዋንጫ መገኛ ምክንያት ሆነዋል፡፡ የቅርብ ተቀናቃኞች ላይ የተገኙት
ውጤቶች ደግሞ ሚናቸው የላቀ ነበር፡፡
ከ1990/91 ጀምሮ 239 ያህል ተጨዋቾች ቀዩን ማሊያ አጥልቀው ክለቡን አገልግለዋል፤ በርካቶችም
በተወዳጆቹ የክለቡ ደጋፎዎች የልብ ቦታ ተችሯቸዋል ፤ በስቴቨን ጄራርድ የቡድን መሪነት ጊዜ እውን
ያልሆነው ግን በሌላኛው እንግሊዛዊ ጆርዳን ሂንደርሰን አምበልነት ተሳክቷል፡፡
በእነዚህ የሶስት አስርት ዓመታት ዘመናት ውስጥ ግን ልዩ ክብር እና ቦታ የሚሰጠው ተወዳጁ ስቴቨን
ጄራርድ ክፉና ደግ ጊዜን ከልጅነት ክለቡ ጋር ቢያሳልፍም የሊጉን ክብር አንዴም ቢሆን ከፍ አለማድረጉ
ቢያስቆጭም፤ በእርሱ ተከታዮች ግን እውን ሆኗል፡፡ ለዚህ ደግሞ የዘንድሮው የቡድን ስብስብ በቀያዮቹ
ልብ ውስጥ በደማቁ መስፈሩ ትክክለኛ እውቅና ነው፡፡

ንጉሱ ሰር ኬኒ ዳልግሊሽ16ኛውን፣ 17ኛውን እንዲሁም 18ኛውን ዋንጫ ለመርሲ ሳይዱ ቡድን
በአሰልጣኝነት ዘመኑ ያጎናፀፈ ሲሆን ከዚያ በኋላ ጊዜያዊው ሮኒ ሞራን፣ ከዚያም በቋሚነት ግራም ሱነስ፣
ሮይ ኢቫንስ፣ ጄራርድ ሁዬ፣ ራፋኤል ቤኒቲዝ፣ ሮይ ሁድሰን፤ ድጋሜ ኬኒ ዳልግሊሽ በመቀጠል ብሬንዳን
ሮጀርስ መጥተው እንደየ ዘመናቸው ቢሆኑም የሊግ ዋንጫው አንፊልድን ሊረግጥ አልቻለም፡፡
በመጨረሻም 9ኛው የርገን ክሎፕ በ2015 የቀያዮቹን ቤት ከረገጠ በኋላ ከዓመት ዓመት አስደናቂ መሻሻል
በማሳየት ፊርማውን ሲያኖር ለቡድኑ ቃል የገባውን አንድ በአንድ ተወጥቶ በመጨረሻም የገዘፈውን ቃል
ጠብቋል፡፡
የመርሲ ሳይዱ ቡድን ከመጨረሻው የሊጉ ድል በኋላ እስራኤላዊውን አጥቂ ሮኒ ሮዘንታልን ከስታንዳርድ
ሌጅ በ1 ሚሊዬን ፓውንድ ክፍያ ከ218ቱ አዲስ ፈራሚዎች አድርጎ ካመጣ ጀምሮ ባለፈው ጥር ወር፤
ለመጨረሻ ጊዜ በ7.25 ሚ/ፓ ክፍያ አንፊልድ እግሩ ከረገጠው ጃፓናዊው ታኩሚ ሚናሚኖ ድረስ 1.47
ቢሊዬን ፓውንድ ፈሰስ አድርጓል፡፡
ከእነዚህ ውስጥ በክለቡ አካዳሚ ከተነሱት ጀምሮ፤ በርካሽ ዋጋ ትልቅ አገልግሎት ከሰጡት እና ከፍ ያለ
ዋጋ ወጥቶባቸው አስቀያሚ ጊዜያትን እስካሳለፉት ድረስ የቀያዮቹ ጉዞ በብርቱ ተፈትኗል፡፡ ያለፉት
ዓምስት ዓመታት የአንፊልድ ስራዎች ከሁሉም የላቀ ውጤትን አስገኝተዋል፡፡
በእነዚህ ሁሉ ዘመናት ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ቢመጡም ቢሄዱም፤ You'll never walk alone
የሚለው የእነዚያ ልባም የቀያዮቹ ደጋፊዎች ዝማሪና ታማኝነት ግን ሳይለዋወጥ ፀንቶ ዘልቋል፡፡ ለዚህም ነው
በሌሎች ተቀናቃኝ ክለቦች ደጋፊዎች ጭምር ክብር የሚሰጣቸው፡፡ ከዚህ ሁሉ ገድል ጀርባ ደግሞ
አስተዋፅኦቸው የማይተካ ነበር፡፡
ከአሊሰን ቤከር የሚነሳው የመርሲ ሳይዱ ስኬት፤ በቫን ዳይክ፣ አርኖልድ እና ሮበርትሰን ብርታት ጎልብቶ፤
በሂንደርሰን እና ጂኒ ዋይናልደም እንዲሁም ሌሎች ዳብሮ፤ በሶስቱ ፊት አውራሪዎች ሳኔ፣ ፊርሚኖ እና ሳላህ
ስልነት በመጨረሻው የሚናፈቀው ክብር እንዲሰምር ሆኗል፡፡
አርትስ ቲቪ// አክሊሉ ማሬ

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button