Africa

ኢጋድ ኢትዮጵያ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተከሰተውን ችግር በሰላማዊ አማራጭ ለመፍታት መወሰኗን አደነቀ፡፡

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 29 ፣ 2014 ኢጋድ ኢትዮጵያ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተከሰተውን ችግር በሰላማዊ አማራጭ ለመፍታት መወሰኗን አደነቀ፡፡
39ኛው የኢጋድ መሪዎች አስቸኳይ ጉባኤ በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና ደህንነት፣ ኢኮኖሚያዊ ትብብር፣ አካባቢያዊና ሀገራዊ ፖለቲካዊ ለውጦች፣ እንዲሁም በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ዙሪያ በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ መክሯል።


የአባል ሀገራቱ መሪዎች የኢትዮጵያ መንግስት ሀገራዊ ምክክር ለማድረግ ያሳየውን ቁርጠኝነትና በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መወሰኑን በአድናቆት እንደሚመለከቱት ገልጸዋል፡፡

መንግስት ወደ ትግራይ ክልል ያልተገደበ ሰብዓዊ ርዳታ እንዲደርስ እያደረገ ያለው ጥረትም በጉባኤተኞቹ ዘንድ በመልካም ጎኑ የታየ ነው ተብሏል፡፡ በጉባኤው የተሳተፉ መሪዎች ባወጡት በጋራ መግለጫ በኢጋድ አባል ሀገራትና በቀጠናው ላይ ተፅዕኖ እየፈጠሩ የሚገኙ ውስጣዊና ውጫዊ የፖለቲካና የደህንነት ችግርችንም በጋራ መቋቋምና ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ስራ መስራት እንደሚገባ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡


መሪዎቹ በድርቅና የተፈጥሮ አደጋዎች ላይ በጥልቀት የመከሩ ሲሆን በቀጠናው ያለውን ከፍተኛ የድርቅ አደጋ ለመመከት የአጭር ጊዜና ዘላቂ መፍትሔዎችን በጋራ በማዘጋጀት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት የተከሰተው የምግብ እጥረት፣ ኮቪድ 19 በጤና ስርዓቱ ላይ የፈጠረው ጫና፣ እንዲሁም በተወሰኑ አካባቢዎች ያለው ከባድ የጎርፍ አደጋ አሳሳቢ በመሆኑ የተቀናጀ አስቸኳይና ዘላቂ ምላሽ መስጠት እንደሚገባም በጉባኤው ተነስቷል፡፡ ዓለም አቀፍ  አጋሮችና የረድኤት ተቋማት ሰብዓዊ ድጋፋቸውን አጠናክርው እንዲቀጥሉ በመሪዎች ጉባኤ ጥሪ ቀርቧል።

Related Articles

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Back to top button