የአዲስ አበባ ከተማ ለቡና እና ጊዮርጊስ ክለቦች የገና ስጦታ አበረከተ
የአዲስ አበባ ከተማ ለቡና እና ጊዮርጊስ ክለቦች የገና ስጦታ አበረከተ
ለኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለቦች የልምምድ እና ስቴድየም መስርያ ቦታ ተበረከተ፡፡
የኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለቦች በተደጋጋሚ የልምምድ መስሪያ ቦታ ችግር እንዳለባቸው እና የማስፋፊያ ቦታ ጥያቄዎችን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሲገልፁ ቆይተዋል፡፡
አዲሱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጥያቄው አግባብነት እንዳለው በማመን ለሁለቱም የከተማዋ ኃያል ክለቦች የልምምድ መስርያ ቦታ ለመስጠት ውሳኔ ላይ የደረሰ መሆኑን እና አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ከቀናት በፊት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢ/ር) ትናንት ማምሻውን ከኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ አመራር እና የክለቡ ደጋፊ ተወካዮች ጋር ባደረጉት ቆይታ ክለቦቹ በተደጋጋሚ ሲያቀርቡ ለቆዩት የልምምድ እና የስታዲዬም መስሪያ ቦታ ጥያቄ የከተማ አስተዳደሩ ምላሽ መስጠቱን እና ክለቦቹ የተሰጣቸውን ቦታ መረከብ እንደሚችሉ አስታውቀዋል፡፡
ታከለ ኡማ “ሁለቱም ክለቦች የከተማችን ብርቅዬ ስጦታዎች ናቸው!” ያሉ ሲሆን የከተማ አስተዳደሩም ሁለቱን ክለቦች በባለቤትነት የሚያይ መሆኑን እና አስፈላጊ በሆነ ሁሉ ከጎናቸው እንደሚቆም ቃል ገብተዋል ሲል የከንቲባ ፅ/ቤት መረጃውን ለአርትስ አድርሷል፡፡