loading
ተወዳጁ አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።

አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም ከ1948-2010
ከመድረኩ ንጉሳችን ፣ንጉሥ ቴዎድሮስን፣ንጉሥ ኤዲፐስን ፣ንጉሥ ሐምሌትን፣ ንጉሥ አርማህን በህይወት አጣናቸዉ፡
መቃብር ቆፋሪውና የሬሳ ሳጥን ሻጩ፣ እሳት ሲነድ፣ ቤቴ፣ የሠርጉ ዋዜማ፣ ደማችን፣ የሊስትሮ ኦፔራ፣ አቡጊዳ ቀይሶ፣ ባለካባ ባለዳባ፣ መልዕክት ወዛደር፣ ታርቲዩፍ ከተወነባቸው ይገኙበታል፡፡
ኪነ ጠቢቡ ፍቃዱ ተክለማርያም በቴሌቪዥን ከተወናቸው ተውኔቶች መካከልም ያልተከፈለ ዕዳ፣ የአበቅየለሽ ኑዛዜ፣ ባለጉዳይና በሕዝብ ዘንድ አድናቆትን ያተረፉለት ናቸው፡፡ ከዚህም ባሻገር ‹‹ከመጻሕፍት ዓለም›› ይባል በነበረው የኢትዮጵያ ሬዲዮ ፕሮግራም ‹‹ሞገደኛው ነውጤ፣ ጥቁር ደም፣ ሳቤላ፣ የነበረው እንዳልነበር›› የተባሉትን አጭርና ረዥም ልቦለዶችን ተውኔታዊ መልክ በመስጠት ቀልብን በሚይዝ የአተራረክ ስልት በመተረክ እንደሚታወቅ የፋንታሁን እንግዳ መዝገበ ሰብ ድርሳን ይገልጸዋል፡፡ ከአራት አሠርታት በላይ በኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ሕይወት ውስጥ ገዝፎ የሚታየው ፍቃዱ ተክለማርያም በፊልም ተዋናይነትም ከግዙፋኑ ከያንያን ተርታ ይሰለፋል፡፡
ከተወነባቸው መካከል አንድ በሆነው “ቀይ ስህተት” በተባለው ፊልምየተዋጣለት ፊልም ለመሥራት በመብቃቱ “አቶዝ” በሚል መጠሪያ የምትታወቀውን መኪና የቴዲ ስቱዲዮ ሽልሞታል::
አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም በ1948 ዓ.ም. አዲስ አበባ ውስጥ በአራት ኪሎ አባወልዴ ችሎት ልዩ ስሙ ጅሩ ሰፈር ተወለደ፡፡
የቄስ ትምህርት ከተማረ በኋላ ከ1ኛ-4ኛ ክፍል ሚያዝያ 27 የግል ት/ቤት ተማረ፡፡
ከ4ኛ -10ኛ ቤተመንግስት የተባለዉ ት/ቤት ተምሯል፡
ፍቃዱ፣ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ከነበረበት ጊዜ አንስቶ ተስፋዬ አበበ መሥርተውት በነበረው የቴአትር ዕድገት ክበብ ውስጥ በነበረው የትወና እንቅስቃሴው እየታወቀ በመምጣቱ በ1967 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ በመቀጠር የተውኔት ጉዞውን መጀመሩ ይነገርለታል፡፡
ፍቃዱን አስደናቂ ተዋናይ ካስባሉት አጋጣሚዎች መካከል የአራት የተለያዩ ነገሥታትን ሚናዎች እየወሰደ የተጫወተው በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ በቴዎድሮስ፣ በሐምሌት፣ በንጉሥ አርማህና በኤዲፐስ ንጉሥ ተውኔቶች የተለያየ ሰብዕና ያላቸውን ነገሥታት ሚናዎች ወስዶ በመጫወቱ ይታወቃል፡፡
ፍቃዱ በአንድ ወቅት የተለያየ ሰብዕና ያላቸውን ነገሥታትን ሚናዎች በመጫወቱ ምን እንደሚሰማው እና ከነገስታቱ ማንን መሆን እንደሚመኝ ለተጠየቀው ጥያቄ ሲመልስ፣ “መቸም ኤዲፐስ መሆን ፍርጃ ነው፡፡ የሃምሌትን ንጉስ ገላውዴዎስን መሆንም አልፈልግም:: ባይሆን ቴዎድሮስንና ንጉስ አርማህን ብሆን አልጠላም” ሲል መልሷል::
በተለይ ለአፄ ቴዎድሮስ ያለውን ክብር ለመግለጽ የሰርጉለት በቴዎድሮስ አደባባይ ተገኝቶ የትያትሩን የተወሰነ ክፍል መነባነብ ላጃቢዎቹ አቅርቦ ነበር::
አርቲስት ፍቃዱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኩላሊት ህመም አጋጥሞት ለጸበል ወደ ስሪንቃ ቅድስት አርሴማ ተጉዞ የነበረ ቢሆንም በህይዎት መመለስ አልቻለም::
ለምንግዜም የጥበብ ባለዉለታችን አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም ህልፈት ማዘናችንን አየገለጽን
አርትስ ቲቪ ለቤተሰቦቹ ለሞያ ባልደረቦቹና ለአድናቂዎቹ መጽናናትን ይመኛል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *